ለሕልውና መታገል ተፈጥሮአዊ ራስን የማስከበር መብት እንጅ ወንጀል አይደለም፤ ወንጀልም በዘር አይተላለፍምና በንጹሃን ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም!

ጋዜጠኛ ዓባይ ዘውዱ -የሕሊና እስረኛ
(ከቂሊንጦ ማ/ቤት)

መቶ አለቃ ውዳለው አንዳርጌ ፈሬ ይባላል። ነዋሪነቱ ምስራቅ ጎጃም ዞን በእናርጅ እናውጋ ወረዳ (ደብረወርቅ) ተንጉማ በተባለ ቀበሌ ነው።

መቶ አለቃ ውዳለው በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ስርዓት እና ስሪት ወለድ ሁለንተናዊ ጥቃት በዝምታ ማለፍ ከጨፍጫፊዎች ጋር እንደመተባበር ይቆጠራል በሚል ወደ ህልውና ትግሉ መቀላቀሉ ተወስቷል።

በዚህ ራስን የመከላከል እና የማዳን ፋኖ መር ህዝባዊ ትግል ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የአማራ ፋኖ በጎጃም የሶማ ብርጌድ ወታደራዊ አዛዥ እንዲሁም የበላይ ዘለቀ ክፍለ ጦር አዛዥ በመሆን የአማራ ህዝብ ህልውና፣ ነጻነት፣ ክብር፣ ሰብዓዊነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነት እና አንድነት ተከብሮ እንደ ዜጋ የሀገር እና የመንግስት ባለቤት በመሆን መብት፣ ጥቅም እና ፍላጎቱ ይከበር ዘንድ የአማራነት እና ሰው የመሆን ግዴታውን እየተወጣ ስለመሆኑ ተገልጧል።

የዚህ የህልውና ታጋይ አባት አቶ አንዳርጌ ፈሬ ይባላሉ። በግምት የ67 ዓመት አዛውንት የሆኑ ጠንካራ እና ለፍቶ አዳሪ አርሶ አደር ስለመሆናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይመስክሩላቸዋል።

እኒህ አባት መቶ አለቃ ውዳለውን ወልደው አሳድገው በማስተማር ለሀገር እና ለወገን ተቆርቋሪ መልካም ዜጋ እንዲሆን የአባትነት ድርሻቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል።

ልጃቸውም አላሳፈራቸውም፤ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን የጅምላ ፍጅት፣ የጦር ወንጀል፣ መፈናቀል እና መሰደድ ይቁም በማለት ይህንን ስርዓት መር አደጋ ለመቀልበስ ሕዝባዊ የህልውና ዘመቻውን በመቀላቀል እየታገለ መሆኑ ተመላክቷል።

ከሕዝባዊ ትግሉ ጎን በመሰለፍም ለነጻነት እና ለክብር መታገሉ-አትግደሉን!-ማለቱ እንደ ወንጀል ተቆጥሮበት ከመሳደዱም ባሻገር በቤተሰቦቹ ላይም ከፍተኛ እና ተደጋጋሚ የሆነ ግፍና በደል ሲፈጸምባቸው ተስተውሏል።

ህዝባዊ ትግል ወንጀል አይደለም፤ የህዝብ ትግል የተነሳለትን አላማ እውን ሳያደርግ ፈቅዶ በመቀበል፣ በፍቅር እና በጥበብ ካልሆነ በስተቀር በተለይ በአፈሙዝ ሊያሸንፈው የሚችል አካልም የለም።

ወንጀል አይደለም እንጅ ቢሆን እንኳ በዘር የሚተላለፍ ስላልሆነ እያንዳንዱ ግለሰብ በሚፈጽማቸው ማናቸውም ተግባራት ራሱ ኃላፊነት መውሰድ ሲገባው በቤተሰቦቹ ላይ ያልተገባ ጫና፣ ወከባና ጥቃት መፈጸም ፍርደገምድልነት ነው፤ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ መሆኑ ነው።

ይህ አካሄድ በደምባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ አይነት የሆነ ደመ ነፍሳዊነት ነው።

አሳዛኙ የግድያ ወንጀል ይህ ነው፦
የእድሜ ባለጸጋው አቶ አንዳርጌ ፈሬ ከቤታቸው ውስጥ በተቀመጡበት አቅደው መጡ በተባሉ የአገዛዙ መከላከያ መር ጥምር ኃይል አባላት አማካኝነት ጥቅምት 16/2017 ንጋት ላይ አፈና ተፈጸመባቸው።

የአገዛዙ ኃይሎች ከተንጉማ የገጠር ከተማ አፍነው ሲወስዷቸውም እንደ ጥፋት የተቆጠረባቸው የመቶ አለቃ ውዳለው አባት መሆናቸው ነው።

“እኛ ጋር ነዎት ወይስ ከልጅዎት ጋር? ከእኛ ጋር ቢሆኑ ኖሮ ልጅዎት እንዲህ ሲታገለን ዝም አይሉም ነበር” በማለት ወደ ጫካ በመውሰድ አሳዛኝ እና ዘግናኝ በሆነ መልኩ ግምባራቸውን በጥይት በመምታት ረሽነዋቸው አስከሬናቸው ተጥሎ ተገኝቷል።

የእድሜ ባለጸጋው አጋሩ፣ መካሩ እና ገባሩም ያለምንም ጥፋታቸው ከመኖሪያ ቤታቸው በጥሪታቸው የገዙት የቤት እና ንብረት መጠበቂያ ትጥቃቸው ተወስዶ በግፍ መገደላቸው በተለይም የአካባቢው ነዋሪዎችን በእጅጉ አስደንግጧል፣ አሳዝኗል፣ አስከፍቷል፣ አስቆጥቷልም ተብሏል።

በመሆኑም በመቶ አለቃ ውዳለው አባት በአቶ አንዳርጌ ፈሬ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ በተለይም እንደ አማራ እንደ አንድ ማሳያ ይሆናል በሚል ካልሆነ በስተቀር በበርካታ አካባቢዎች እንዲህ አይነት ስርዓትና መንግስት መር የሆኑ ወንጀሎች ያለምንም ተጠያቂነትና በማናለብኝነት ተፈጽመዋል፣ እየተፈጸሙም ነው።

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖችን በተመለከተ እንዲያው በደፈናው ሆድ ይፍጀውና ቤት ይቁጠራቸው ከማለት ውጭ ዘርዝሮ ለማስቀመጥ ከብዛት እና ከጊዜ አንጻር የሚቻል አይደለም።

የእኒህ የተከበሩ የሀገር ባለውለታ አርሶ አደር አስከሬንም ከጥቃት በተረፉ የሐይማኖት አባቶችና የሐገር ሽማግሌዎች በእለቱ ጥቅምት 16/2017 እንዲነሳ ተደርጎ በተንጉማ ማሪያም ስርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

በእርግጥ ስርዓታዊ የሆነ ይፋዊ ጦርነት ለተከፈተበትና ሞትን ለለመደው ለስርነቀል ስርዓታዊ ለውጥ እየታገለ ላለው ለሰፊው የአማራ ህዝብ እንዲህ አይነት ልብ ሰባሪ እና አሳዛኝ የግድያ ዜናዎች መስማት አዲሱ አይደለም።

እንዲህ አይነት አሰቃቂና አረመኔያዊ የሆኑ የወንጀል ድርጊቶች በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ብሎም ከክልሉ ውጭ በሚኖሩ አማራዎች ላይ ማንነታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በኦህዴድ መራሹ የብልጽግና አገዛዝ፣ ስርዓቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስልታዊ በሆነ መልኩ ይደግፋቸዋል በተባሉ የሽብር ቡድን አደረጃጀቶች በምድርም ሆነ በአየር ኃይል ጭምር በተናጠልም ሆነ በጅምላ ቢያንስ ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር በላይ በአዋጅም ሆነ ያለ አዋጅ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሁሉን አቀፍ ጥቃት ተከፍቶበት በየቀኑ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ላለ ማህበረሰብ አዲስ ላይሆን ይችላል፤ ግን ደግሞ እንደ ሰው ለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ለመላው አማራ እና ለሰው ልጆች ሁሉ የደም እምባ ሊያስለቅስ የሚችል አሳዛኝ የወንጀል ድርጊት ነው ለማለት ይቻላል።

በእርግጥ ይህ ፍጹም ኃላፊነት ከማይሰማው አረመኔያዊ ጸረ ህዝብ እና ጸረ ሀገር፣ በስልጣን ጥም በሽታ ከናወዘ፣ በጥላቻና በሀሰት ትርክት ከታወረ፣ ከራሱ ውጭ ሕዝብን የማይሰማ፣ አምባገነን ግን ደግሞ ዱላው 12 ከሆነ ፈሪና ድንጉጥ ከሆነ አገዛዝ የሚጠበቅ የወንጀል ድርጊት ነው።

መረጃዎች እንዳመለከቱት ለህጻናት፣ ለሴቶች እና ለአቅመ ደካሞች እንኳ እንጥፍጣፊ ሰብዓዊ ርህራሄ በተነጠቀው አገዛዝ በተላከው መከላከያ በሸዋ በረኸት ወረዳ መተህብላ አካባቢ ወ/ሮ አስበራ መሃመድ የተባች እናት የ3 ዓመት ህጻን ልጇን እንዳዘለች ጥቅምት 1/2017 በአሰቃቂ መልኩ ተገድላ ህጻን ልጇ ከእናቱ አስከሬን አጠገብ መሬት ላይ ወድቆ ለአሞራ እና ለዱር አውሬ ተጋላጭ ሆኖ “እማ!” እያለ ሲጣራ እና ሲያለቅስ ከመስማት እና እንባው ሲፈስ ከማየት በላይ ምንስ አስከፊና ሰው መሆንን የሚፈትን ልብ ሰባሪ ሀዘን አለ?

በእናት ሆድ ውስጥ ላለ ጽንስ ማንነት ተሰጥቶት ነፍሰ ጡር እናት በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ሆዷ ተቀዶ ጽንሱ እንዲወጣ ሲደረግ፣ አንገቷም ተገዝግዞ ታርዳ ስትገደልና አካላቸው ተቆራርጦ አንድ ላይ ሲከመር ማየት ያማል!

ክቡር የሆነው የሰው ልጅ አስከሬን የአሞራ እና የዱር አውሬ ሲሳይ ሲሆን ሰዎች ከእነ ነፍሳቸው በገደልና በውሃ ውስጥ ተወርውረው ሲጣሉና ሲገደሉ ማየትና መስማት በእጅጉ ይፈትናል!

በጅምላ ተፈርጀውና የማጥቂያ ኮድ ተሰጥቷቸው ከተሳፈሩበት መኪና እንዲወርዱ ተደርጎ መታዎቂያቸው እየታየ የተገደሉትና ደብዛቸው እንዲጠፋ የተደረጉት ወገኖችን ማሰብ ውስጥን ያደማል!

እናት በአንቀልባዋ ያዘለችው ልጇ በአልሞ ተኳሾች ጀርባዋ ላይ ሲገደልባት፣ እናት ህጻን ልጇ ከአጠገቧ በጨካኞች ታፍና እና ታግታ ስትወሰድ፣ ስትደፈርና በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ ስትጣልባት አስከፊነቱን እናስበው!

እናትና ልጅ፣ አባትና ልጅ፣ ወንድማማቾች፣ እህትማማቾች በግፍ ሲገደሉ፣ በትራንስፖርት የሚጓዙ ንጹሃን በድሮን ከመቅጽበት ወደ አመድነትና ቁርጥራጭነት ሲቀየሩ፣ በጤና ተቋማት ህክምና የሚከታተሉ ህሙማን ከእነ አስታማሚያቸው ሲገደሉ እንዲሁም ከጤና ተቋም ወጥታ ወደ ቤቷ የምትጓዝ አራስ እናት ተገድላ ጨቅላ ህጻኗ ያለ እናት ስትቀር ማየት ከባድ ነው ወገን!

በርካቶች ወላጆች ተገድለው ልጆችና ቀሪ ቤተሰቦቻቸው ሲበተኑ፣ ልጆቻቸው ተገድለው ወላጆች ያለጧሪና ቀባሪ ሲቀሩም ተስተውሏል።

በመኖሪያ ቤታቸው እና በእምነት ተቋማት (በቤተ ክርስቲያን፣ በመስጊድ— ) ለአምልኮ በተሰበሰቡበት ጭካኔ በተመላበት መልኩ በጅምላ ሲደፈሩ፣ ሲጨፈጨፉና በእስካቫተር ተቆፍሮ በአንድ ጉድጓድ በጅምላ ሲቀበሩ ማየት በተለመደበት፣ በማያስደነግጥበት፣ ተጠያቂነት እና የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ሰፊው የአማራ ህዝብ እየተፈተነ ነው።

ተማሪዎች ለመማር በሄዱበት ትምህርት ቤት ላይ ሲገደሉና ታፍነው ደብዛቸው ሲጠፋ፣ ገበሬ ከእነ በሬው እርሻ ማሳው ላይ ተገድሎ ሲገኝ፣ ከግማሽ በላይ ቤተሰብ ሲገደልባቸው፣ መላ ቤተሰባቸውን በግድያና በስደት አጥተው ብቻቸውን ሲቀሩ አሰቃቂነቱን አስቡት!

በከባድ ምርመራ እና ድብደባ ሲገደሉ፣ በስውር ቦታ ሲታገቱ፣ አካላቸው ሲጎድልና ተንኮላሽተው ዘር እንዳይተኩ ሲደረጉም ተመልክተናል።

አረብ አገር ጭምር ተሰደው ጥረው ግረው ባገኙት ገንዘብ የሰሩት ቤታቸው በማንነታቸው የተነሳ በህግ ሽፋን ያለምንም ምትክና ካሳ ፈርሶ ሲፈናቀሉ ቤታቸውም በላያቸው ላይ በእስካቫተር፣ በግሬደርና ሎደር ሲፈርስባቸው ሰሚ አጥተው የደም እንባ ሲያነቡ ማየት ሰው መሆንን ይፈታተናል!

አንዳንዶችም ቤታቸው በመፍረሱ ተስፋቸው ተሟጦ፣ መሄጃ አጥተው ሜዳ ላይ ተቀምጠው ሲታዩና ይህ የእናንተ አይደለም በሚል የመቆሚያና የማረፊያ ጎዳና ሲነፈጋቸው፣ በጅብ ተበሉ የሚል አሳዛኝ ዜና መስማታችንም ይታወሳል።

በአገዛዙ ወንበዴዎች ንብረታቸው ተዘርፎ ቤታቸው ሲቃጠል በብስጭት ራሳቸውን ሲስቱ፣ ሲያብዱና ራሳቸውን ሲያጠፉ ማየትም ተፈጽሟል።

በማንነታቸው ታግተው ተሰውረው ፍትሕ ሲነፈጋቸው፣ የሀገር እና የፖሊሲ ሉዐላዊነት ሲደፈር፣ ከህግ ይልቅ የግለሰብና የአገዛዝ የበላይነት ሲሰፍን፣ አውሬያዊነት፣ ደመ ነፍሳዊነትና ስሜታዊነት ሲነግስ እያዬንም ነው!

ነጻነት፣ ክብር፣ ማንነት፣ እኩልነት፣ አብሮነት እና ሰብዓዊነት ተገፎ የመኖር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በጅምላ ሲፈናቀሉና ለሰው ሰራሽ ርሀብ ሲጋለጡ፣ በርካቶች ከዘረኛ አምባገነን ስርዓት ጥቃት በመሸሽ በስደት የዱር አውሬና የባሕር ሲሳይ ሲሆኑ ተመልክተናል።

የብልሹ አሰራር መንሰራፋት ፣ የሞራል መላሸቅ፣ ባህልና እሴቶች አለመከበር፣ ራስ ናቂ ውጭ አድናቂነት በሰፈነበት ከምንም በላይ ደግሞ አያሌ ዜጎች ሀገርና መንግስት አልባ ሆነው ተቅበዝባዥ እና ተስፋ ቆራጭ እንዲሆኑ በሁኔታዎች በተገደዱበት ሀገር አለመፈተን አይቻልም።

የሀሳብ ብክለትና ድርቀት በዝቶ መወያየት፣ መደማመጥ፣ መከባበርና መቻቻል በጠፋበት ሁኔታ፣ የሀሰት ትርክትና ጥላቻ መንግስታዊ መመሪያ በሚመስል መልኩ በሚያገለግልበት፣ እንዲሁም ህግ፣ ስርዓት፣ ስሪትና ተቋማት ዜጎችን በማንነት ለይቶ ለማጥቃት እንደ መሳሪያ ሆነው የሚያገለግሉበትን ነባራዊ ሁኔታም መዘንጋት የለበትም።

ሴረኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ዘረኝነት፣ እርስ በርስ መገፋፋትና መጠፋፋት በበዛበት ለዚህ ሁሉ ችግር የመፍትሔ አማራጩ አፈ ሙዝ ወይም ጉልበት ነው ብሎ በማመን በህዝብ ላይ ይፋዊ ጦርነት ከፍቶ ሁሉ ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚል ስርዓትና ስሪት በነገሰባት ሀገር ኢትዮጵያ አማራ እንደ ህዝብ ባይፈተን እና ይህን ሰቆቋ ለማስቆም ባይታገል ነው የሚገርው።

የአቶ አንዳርጌ ፈሬንና የመሰል ንጹሃን ሰማዕታትን ነፍስ ይማር!

ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እንመኛለን!

ለሕልውና መታገል ተፈጥሮአዊ ራስን የማስከበር መብት እንጅ ወንጀል አይደለም፤ ወንጀልም በዘር አይተላለፍምና በንጹሃን ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም!

ፍትሃዊ የሆነው የአማራ የህልውና ትግል ያሸንፋል!